Amharic Bible

መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ።
Chapter 1 of 36
left-arrow Chapter - 1 right-arrow
Verse 1

የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በመንግሥቱ በረታ፤ አምላኩም እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረ፥ እጅግም አገነነው።

Verse 2

ሰሎሞንም ለእስራኤል ሁሉ፥ ለሻለቆች፥ ለመቶ አለቆችም፥ ለፈራጆችም፥ በእስራኤልም ሁሉ ዘንድ ለነበሩ መሳፍንት ሁሉ፥ ለአባቶች ቤቶች አለቆች ተናገረ።

Verse 3

ሰሎሞንም ከእርሱም ጋር ጉባኤው ሁሉ የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ በምድረ በዳ የሠራው የእግዚአብሔር መገናኛ ድንኳን በዚያ ነበረና በገባዖን ወዳለው የኮረብታ መስገጃ ሄዱ።

Verse 4

ለእግዚአብሔር ታቦት ግን ዳዊት በኢየሩሳሌም ድንኳን ተክሎለት ነበርና ዳዊት ከቂርያትይዓሪም ወዳዘጋጀለት ስፍራ አምጥቶት ነበር።

Verse 5

የሆርም ልጅ የኡሪ ልጅ ባስልኤል የሠራው የናስ መሠዊያ በዚያ በእግዚአብሔር ማደሪያ ፊት ነበረ፤ ሰሎሞንም ጉባኤውም ይህን ይፈልጉት ነበር።

Verse 6

ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት በመገናኛው ድንኳን አጠገብ ወዳለው ወደ ናሱ መሠዊያ ወጣ፥ በዚያም አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አቀረበ።

Verse 7

በዚያም ሌሊት እግዚአብሔር። ምን እንድሰጥህ ለምነኝ ሲል ለሰሎሞን ተገለጠ።

Verse 8

ሰሎሞንም እግዚአብሔርን አለው። ከአባቴ ከዳዊት ጋር ታላቅ ምሕረት አድርገሃል፥ በእርሱም ፋንታ አንግሠኸኛል።

Verse 9

አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ፥ ቍጥሩ እንደ ምድር ትቢያ በሆነው በብዙ ሕዝብ ላይ አንግሠኸኛልና ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸው ተስፋ ይጽና።

Verse 10

አሁንም በዚህ ሕዝብ ፊት እወጣና እገባ ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ስጠኝ፤ ይህን በሚያህል በዚህ በታላቅ ሕዝብ ላይ ይፈርድ ዘንድ የሚችል የለምና።

Verse 11

እግዚአብሔርም ሰሎሞንን። ይህ በልብህ ነበረና፥ ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንና የጠላቶችህን ነፍስ ረጅምም ዕድሜን አልለመንህምና፥ ነገር ግን ባነገሥሁህ በሕዝቤ ላይ ለመፍረድ ትችል ዘንድ ጥበብንና እውቀትን ለራስህ ለምነሃልና ጥበብንና እውቀትን ሰጥቼሃለሁ፤

Verse 12

ከአንተ በፊትም ከነበሩት ከአንተም በኋላ ከሚነሡት ነገሥታት አንድ ስንኳ የሚመስልህ እንዳይኖር ባለጠግነትንና ሀብትን ክብርንም እሰጥሃለሁ አለው።

Verse 13

ሰሎሞንም በገባዖን ካለው ከኮረብታው መስገጃ ከመገናኛው ድንኳን ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ በእስራኤልም ላይ ነገሠ።

Verse 14

ሰሎሞንም ሰረገሎቹንና ፈረሰኞችን ሰበሰበ፥ አንድ ሺህም አራት መቶ ሰረገሎች፥ አሥራ ሁለት ሺህም ፈረሰኞች ነበሩት፤ በሰረገሎች ከተሞችና ከእርሱ ጋር በኢየሩሳሌም አኖራቸው።

Verse 15

ንጉሡም ብሩንና ወርቁን በኢየሩሳሌም እንደ ድንጋይ እንዲበዛ አደረገው፤ የዝግባም እንጨት ብዛት በቈላ እንደሚበቅል ሾላ ሆነ።

Verse 16

ሰሎሞንም ፈረሶችን ከግብጽና ከቀዌ አስመጣ፤ የንጉሡም ነጋዴዎች በገንዘብ እየገዙ ከቀዌ ያመጡአቸው ነበር።

Verse 17

አንዱም ሰረገላ በስድስት መቶ፥ አንዱም ፈረስ በመቶ አምሳ ሰቅል ብር ከግብጽ ይወጣ ነበር፤ እንዲሁም ለኬጢያውያንና ለሶሪያ ነገሥታት ሁሉ በእጃቸው ያመጡላቸው ነበር።

Chapter -
1